Sunday 31 March 2013


ኩዌት ከኢትዮጵያ የሚመጡ ሠራተኞችን አልቀበልም አለች


ኩዌት በቅርቡ የሕክምና ምርመራ እንዲከናውኑ ተብለው በተመለመሉ አዳዲስ ክሊኒኮች አማካይነት አልፈው የሚመጡ ኢትዮጵያዊያን ሠራተኞችን ወደ አገሯ እንደማታስገባ አስታወቀች፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኘው የኩዌት ኤምባሲ መጋቢት 11 ቀን 2005 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ፣ ኩዌት ወደ ባህረ ሰላጤው አገሮች የሚሄዱ ሠራተኞች የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ በቅርቡ ለተመለመሉ አዳዲስ ክሊኒኮች ዕውቅና አልሰጠችም፡፡

ኩዌት ኤምባሲ በዚሁ ደብዳቤው እንደገለጸው፣ ራሱ ሌላ ማረጋገጫ ደብዳቤ እስካልጻፈ ድረስ የክሊኒኮችን ሥራ የሚያስተባብረው ጋምካ የተባለው አስተባባሪ ተቋም አንድም ተመርማሪ ሠራተኛ በቅርቡ ምርመራ እንዲያካሂዱ ወደተመደቡ የጤና ማዕከላት እንዳይልክ አሳስቧል፡፡

የባህረ ሰላጤው አገሮች ማኅበራት (Gulf Cooperative Council) አባላት ሳውዲ ዓረብያ፣ ኩዌት፣ ኦማን፣ ባህሬን፣ ኳታር፣ የመንና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስን የሚያጠቃልል ሲሆን፣ የእነዚህ አገሮች የጤና ሚኒስትሮች በበኩላቸው የራሳቸውን ማኅበር አቋቁመው በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡

የጤና ሚኒስትሮቹ ማኅበሩ ባለሙያዎችን ወደ አዲስ አበባ በመላክ በከተማው ውስጥ የሚገኙትን ክሊኒኮች ከገመገመ በኋላ አልአፍያ ከፍተኛ ክሊኒኮች፣ አልያንስ ሜዲካል ክሊኒክ፣ ቶዝ ከፍተኛ ክሊኒክ፣ ወሰን ከፍተኛ ክሊኒክ፣ ቤተዛታ ከፍተኛ ክሊኒክ፣ ኦአይሲሶ ስፔሻላይዝድ ክሊኒክ፣ ሜዲገልፍ የጤና አገልግሎትን የመረጠ ሲሆን፣ ኩዌት ለጊዜው በእነዚህ ክሊኒኮች ተመርምረው የሚመጡ ሠራተኞችን እንደማትቀበል ገልጻለች፡፡

ከዚህ በፊት በጤና ሚኒስትሮቹ ተመርጠው ከግንቦት 2000 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ባህረ ሰላጤ አገሮች ለሥራ የሚሄዱ ሠራተኞች ጤና ለመመርመር አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩት አርሾ ሜዲካል ላቦራቶሪ፣ ቢታንያ ከፍተኛ ክሊኒክ፣ ሃሌሉያ ከፍተኛ ክሊኒክ፣ ኬቲ ቅዱስ ገብርኤል ከፍተኛ ክሊኒክ፣ ሰንቴ ከፍተኛ ክሊኒክ፣ ዘንባባ ከፍተኛ ክሊኒክ፣ ዛክ ከፍተኛ ክሊኒክና ሳይመን ከፍተኛ ክሊኒክ ነበሩ፡፡ ምንጭ ሪፖርተር

No comments:

Post a Comment