Friday 29 March 2013


የመድኃኒዓለም መሰናዶ ት/ቤት ተማሪዎች በፖሊስ ተደበደቡ


  • digg
  • 19
     
    Share
ካሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ የመድኃኒያለም መሰናዶው ትምህርት ቤት አስተዳደር በትምህርት ገበታቸው ላይ በሰዓቱ መገኘት ያልቻሉ ተማሪዎችን በትምህርት ቤቱ ደጃፍ እንዳይቆሙ፣ ቆመው ቢገኙ ግን በጸጥታ ሀይል እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ማስጠንቀቁን ተከትሎ በተማሪዎቹና በአስተዳደሩ መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር መነሻ ሆኗል፡፡
ከዚህ ቀደም ተማሪዎች ከጠዋቱ ሁለት ተኩል ጀምሮ እሰከ ለሶስት አስር ጉዳይ ወደ ግቢ መግባት ይፈቀድላቸውና ትምህርት በሶስት ሰዓት ይጀመር የነበረ ቢሆንም አዲሱ ደንብ የትምህርት መጀመሪያ ሰዓትን ወደ ሁለት ተኩል በማውረድ ግቢ ውስጥ ተማሪዎች እስከ ሁለት ከሃያ እንዲገቡ ያዛል፡፡
መድሃኒዓለም ትምህርት ቤት የሚገኝበት አካባቢ መንገድ በጥገና ላይ የሚገኝ ከመሆኑም በላይ  ራቅ ካሉ አካባቢዎች ማለትም ከፈረንሳይ ለጋሲዮንና ከቡራዮ የሚመጡ ተማሪዎች በትራንስፖርት ችግር በአዲሱ ደንብ መሰረት በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት አልቻሉም፡፡ ሰኞና ማክሰኞ ማለዳ ወደ ትምህርት ቤቱ በማቅናት የጉዳዩን ተዋናዮች ለማናገር ጥረት ያደረጉ የፍኖተ ነጻነት ባልደረቦች ዩኒፎርም የለበሱ ተማሪዎች በፖሊሶች ሲባረሩ ተመልክተዋል፡፡ አንዳንድ ተማሪዎችም ጓደኞችቸው እየተያዙ በፖሊስ መኪኖች መጫናቸውን ለባልደረቦቻችን ተናግረዋል፡፡
ከፖሊስ ሽሽት የያዙ ተማሪዎችን በማግኘት ስለ ችግሩ እንዲነግሩን በጠየቅንበት ሰዓት ስማቸውንና ምስላቸውን እንዳንጠቀም በመማጸን ‹‹ችግሩን የፈጠረው የትምህርት ቤቱ ነው፡፡ የመንገድና የትራንስፖርት ችግር የሌለ ይመስል ርህራሄ በጎደለው መልኩ ሶስትና አራት ታክሲዎችን እየተጠቀሙ የሚመጡ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት እንዳይገቡና ለፈተና እንዳይቀመጡ ማድረግ ሀላፊነት የጎደለው ተግባር ነው፡፡ የፖሊስ አባላት በተማሪው ላይ እርምጃ ከመውሰድ በፊት የችግሩ ምንጭ ምን እንደሆነ ለማወቅ ጥረት አለማድረጋቸው ነገሩን ወደ ማይፈለግ ሁኔታ እየወሰደው ነው፡፡››ብለዋል፡፡
የትምህርት ቤቱን አስተዳደር በጉዳዩ ዙሪያ  ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ ይሁንና በቅርቡ በአዲስ አበባ አስተዳደር ስር የሚገኘው የሴቶች ጉዳይ 900.000 ብር ወጪ እንዳደረገበት በጠቀሰበት የጥናት ሪፖርቱ በከተማይቱ እየተስፋፋ ለመጣው የአደገኛ  እጽ ተጠቃሚነት ትምህርት ቤቶች አርፍደው የመጡ ተማሪዎቻቸውን ለማስገባት ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸው ስለመሆኑ መጠቆሙ አይዘነጋነም፡፡
ምንጭ ፍኖተ ነጻነት 

No comments:

Post a Comment