Monday 25 March 2013

‘‘ኢትዮጵያ’’ እያሉ ሲሞሉ የግድ ጎሳችሁን ካልተናገራችሁ.......አራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከተወሰዱ በኋላ ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደርጎ ያለፈቃዳቸው ፎቶግራፍ እንዲነሱ መደረጉን፣ በመቀጠል በእስር ላይ የነበሩት ወጣቶች ‘‘ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻን ደም፤ ኢትዮጵያ ሀገሬ የደፈረሽ ይውደም’’ ሲሉ እዛው ፖሊስ ጣቢያው ውስጥ መዘመራቸውን፣ መዝሙሩን ፖሊሶቹ ሳይቀሩ መዘመራቸውን የሚገልፁት ኢንጂነር ይልቃል ከዚያ ውጪ በፖሊስ መምሪያው አሳፋሪ ተግባር ተፈፅሞ ነበር ይላሉ። የፓርቲው ፕሬዝዳንት ‘‘ቃል በሰጠንበት ወቅት ‘‘ብሔር’’ የሚለው መጠይቅ ላይ ብዙዎቹ ‘‘ኢትዮጵያ’’ እያሉ ሲሞሉ የግድ ጎሳችሁን ካልተናገራችሁ በሚል የደህንነት መርማሪዎቹ ድብደባ ፈፅመዋል። ቃል ሰጥተው ሲወጡ ፊታቸው ያበጠ እና ደም በደም የነበሩ ወጣቶች ነበሩ። ከነዚህም መካከል ብርሃኑ ተክለያሬድና ጌታነህ ባልቻ የተባሉ ደግሞ የፌስቡክ የሚስጥር ኮድ ቁጥራቸውን አምጡ በሚል መገደዳቸውን፣ በህገ-መንግስቱ የአንድ ሰው የግል ምስጢሮቹ ሰነዶቹ አይመረመሩም ቢልም በቀበሌ መታወቂያ ለሚወጣ ተራ ወንጀል የግል ምስጢር ካላመጣችሁ በማለት ድብደባ እስከመፈፀም ደርሰዋል’’ ሲሉ ነው የተናገሩት። ወደፊትም በደብዳቢዎቹ ላይ ክስ ለመመስረት ማስረጃ እየተሰበሰበ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል።

‘‘የመንግስትን ተቋም ተጠቅመው ውንብድና የፈፀሙብን አካላት አሉ’’ ያሉት ኢንጂነር ይልቃል ‘‘ድርጊቱ አፈና ነው። አፈናው ደግሞ ከኢህአዴግ ሕገ-ወጥነትና ሀገሩን ማስተዳደር ካለመቻሉ ጋር የተያያዘ ነው። ኢህአዴግ የሰዎችን መብት እየጨፈለቀ እድሜውን ማራዘም ፈልጓል። ኢህአዴግ ዜጎች መብታቸውን እያረጋገጡ በሄዱ ቁጥር የውስጥ ባዶነቱ እየተጋለጠና ስልጣኑን የሚያጣ እየመሰለው የሚያደርገውን የማያውቅ ስርዓት ሆኖብናል’’ ሲሉ ተናግረዋል።
ከሰንደቅ ጋዜጣ የተወሰደ

No comments:

Post a Comment