Saturday 30 March 2013


በአፋር የተከሰተው ርሃብ ተባብሷል -የሟቾች ቁጥር 22 ደርሷል


5141726825_1b9dcf84f2






በክልሉ ዞን ሁለት አሚባራ ወረዳን ጨምሮ በዞን አንድ በሚገኙት ኤረርሲ፣ ኤልዳዓልና ቢሩ ወረዳዎች የተከሰተው ርሃብ ተባብሶ በመቀጠሉ የሟቾች ቁጥር እያሻቀበ መሄዱን ምንጮቻችን በተለይ ለፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ገልፀዋል፡፡ በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ አፋር ክልል በተከሰተው በዚህ ርሃብ የሟቾች ቁጥር 22 መድረሱ ተሰምቷል፡፡
የአፋር ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የስራ ሂደት ሃላፊ የሆኑት አቶ መሐመድ ያዮ ርሃብ በአካባቢው ጠረፋማ ወረዳዎች የተከሰተው በዋነኝነት በውሃ እጥረት ቢሆንም የምግብ እጥረቱም አለ፡፡ የክልሉ መንግስት 2 ሚሊዮን ብር በመመደብ ውሃ በቦቲ ተሸከርካሪ እየወሰደ ለአካባቢው ማኀበረሰብ እያደረሰ ነው፣ ምግብ ግን በበቂ ሁኔታ በመጋዘናች ተከማችቶ የሚገኝ በመሆኑ እየተሰጣቸው ከመሆኑም በተጨማሪ በአካባቢው ያሉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም የበሰሉ አልሚ ምግቦችን እያዳረሱ ነው፡፡ በአሁን ወቅት ግን በአካባቢው ዝናብ በመዝነቡ የውሃውን እጥረት ችግር መቀረፉንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የእንሰሳቱን የውሃና የምግብ እጥረት ችግር ለመቅረፍ አጎራባች የአማራ ክልል ወረዳዎች ጥሩ ትብብር እያደረጉልን ቢሆንም አብዛኛው አጎራባች ቦታ ተክሎች ተተክለው በአጥር በመከለሉ ለፀጥታ ችግር ሊፈጥር ይችላል በሚል ማሳሰቡ እንዳልቀረ ገልፀውልናል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ታረቀኝ ፅጌ በበኩላቸው በሶማሌና አፋር በተለያየ ጊዜ ድርቅ ስለሚከሰት በቂ የሆነ የምግብ ክምችት ስላለን ወደ ስፍራው ተልኳል፡፡ የተከሰተውም ድርቅ እንጂ ርሃብ አይደልም ሲሉ አክለዋል፡፡
ሆኖም ለፍኖተ ነፃነት የሚደርሱ መረጃዎች እንዳመለከቱት ከሆነ በአካባቢው ያለው ርሃብ እየተባባሰ ወደ አጎራባች ወረዳዎችም ተዛምቷል፡፡ ፍኖተ ነፃነት ባለፈው ሳምንት በክልሉ ዞን አንድ ቢሩና ኤልዳዓል ወረዳ በተከሰተው ርሃብ የ 7 ሰዎች መሞታቸውን መዘገቧ የሚታወስ ሲሆን አሁን ግን ኤረርሲ የሚባል ሌላ ወረዳም ችግሩ በመከሰቱ የሟቾች ቁጥር ወደ 20 መድረሱ ተጠቁሟል፡፡

ምንጭ  ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment